
የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ




የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ
ነገረ ቅዱሳን
የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ህፃናት




የጸሎት ቤት/ለሕፃናት/
ልጆችዬ እንኳን ለዐቢይ ጾም ሦስተኛ ሳምንት በሰላም አደረሳችሁ፡፡ ይህ ሦስተኛው ሳምንት ምኲራብ ተብሎ ይጠራል፡፡ ዛሬ የምንማረውም ትምህርት በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ሁለት ከቁጥር 12 እስከ 17 ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያን ማለት የክርስቲያኖች ቤት ማለት ነው፡፡ የእግዚአብሔር ልጆች በአንድነት ተሰብስበው እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑበት፣ ከእግዚአብሔር ጋር የሚነጋገሩበት ቤት ስለሆነች የጸሎት ቤት ወይም የእግዚአብሔር ቤት እየተባለች ትጠራለች፡፡
በአንድ ወቅት ምን ሆነ መሰላችሁ፥ ጌታችን መድኀኒታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ቅዱሳን ሐዋርያትን ይዞ ወደ ምኲራብ መጣ፡፡ በድሮ ጊዜ ምኲራብ ትባል ነበር፤ አሁን ግን ቤተ ክርስቲያን ተብላ ትጠራለች፡፡ ጌታችንም ወደ ምኲራብ ሲገባ በቤቱ ዙሪያ ብዙ ነጋዴዎች፣ ሻጮች እና ለዋጮች ግቢውን ሞልተው ሲሸጡ ሲነግዱ አያቸው፡፡ አንዳንዱ በሬ ይሸጣል፣ ሌላው በግ፣ ሌላው ዶሮ፣ ሌላው ደግሞ እርግብ…. እየሸጡ የጸሎት ቤት የነበረውን የእግዚአብሔርን ቤት የገበያ ቦታ አደረጉት፡፡ የሰዎቹ ድምጽ፣ የእንስሳቱ ጩኸት ብቻ ምን ልበላችሁ ግቢው በጣም ተረብሿል፡፡ በዛ ላይ አንዳንዶቹ ይጣላሉ፣ ይሰዳደባሉ፣ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ሆነው ክፉ ነገርን ይነጋገራሉ፡፡
አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔርን ቤት ንቀው የጸሎት ቤት የሆነችውን መቅደስ የገበያ ቦታ እንዳደረጉት ሲመለከት ወዲያው ረጅም ጅራፍ ሠራ፡፡ በጅራፉም እየገረፈ በሬዎቹን በጎቹን ሁሉንም ከግቢ አስወጣቸው፡፡ በታላቅ ቃልም ጮኸ “ቤቴ የጸሎት ቤት ናት፥ እናንተ ግን የንግድ ቤት፣ የወንበዴዎች መደበቂያ አደረጋችሁት” ብሎ በአለንጋ እየገረፈ አባረራቸው፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስም ሁሉንም አስወጣ ጸጥታ ሆነ ለተሰበሰቡት ሕዝብ ካሁን በኋላ እንዲህ አታድርጉ፡፡ በእግዚአብሔር ቤት መጸለይ፣ መስገድ፣ መዘመር፣ መማር እንጂ መሸጥ፣ መግዛት፣ መረበሽ፣ መሳደብ፣ መጣላት፣ ክፉ ነገር ማድረግ መጮኸ አይፈቀድም ብሎ አስተማራቸው፡፡ ሕዝቡም አጥፍተናል ይቅርታ አድርግልን ሁለተኛ ይህን ጥፋት አናጠፋም ብለው ቃል ገቡ፡፡
ከዚያም ለተሰበሰቡት የእግዚአብሔር ልጆች ያስተምራቸው ጀመረ፡፡ የሚማሩትም ሰዎች በጣም ደስ ብሎዋቸው ከእግሩ ሥር ቁጭ ብለው ተማሩ፡፡ ዐይናቸው የማያይላቸው ሰዎችም ወደ እርሱ ቀርበው አምላካችን ሆይ እባክህ አድነን ሲሉት፣ እጁን ዘርግቶ ዐይናቸውን ሲነካው ሁሉም ማየት ጀመሩ፡፡ የታመሙ ሰዎች ሁሉ ወደ እርሱ መጡ፣ ሁሉንም አዳናቸው፡፡
ልጆችዬ በእግዚአብሔር ቤት በቤተ ክርስቲያን ስንገባና ስንወጣ ተጠንቅቀን መሆን እንዳለብን አስተዋላችሁ አይደል፡፡ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ቤት የተቀደሰና፣ ሁሌም መላእክት እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑበት የተባረከች ንጽህት ሥፍራ ስለሆነች ነው፡፡ ልጆችዬ ወደ ቤተ ክርስቲያን ስንገባም ሆነ ስንወጣ ተጠንቅቀን ሌሎችን ሳንረብሽ፣ ሳንሮጥ፣ ሳንጮኸ መሆን አለበት፡፡ በሰንበት ትምህርት ቤትም ከወንድሞቻችንና ከእኅቶቻችን ጋራ ስለ እግዚአብሔር እየተነጋገርን፣ እየተማማርን ልናሳልፍ ይገባናል፡፡
እግዚብሔር አምላካችን በቅድስናና በንጽሕና በቤተ ክርስቲያን እንድንኖር ይርዳን አሜን፡
የነነዌ ህዝቦች (ለህጻናት)
በአንድ ወቅት ስሙ ዮናስ የተባለ ሰው ነበር፡፡ ከእለታት አንድ ቀን እግዚአብሔር አምላክ ለዮናስ እንዲህ አለው፡፡ «ወደ ነነዌ ከተማ ሂድ ለሕዝቡም በምትሰሩት የኃጢዓት ሥራ በጣም አዘኜባችኋለሁ፡፡ ይኼንን የምትሠሩትን ሥራ ካላቆማችሁ ከተማዋን አጠፋታለሁ» ብለህ ንገራቸው አለው፡፡ ነገር ግን ዮናስ እግዚአብሔር ያዘዘውን ማድረግ አልፈለገም፤ እየሮጠ ማምለጥ እና ከእግዚአብሔር መደበቅ ፈለገ ስለዚህም ዮናስ ከነነዌ ከተማ በተቃራኒው ወደ ምትገኘው አገር በመርከብ መሔድ ጀመረ፡፡እግዚአብሔርም በባሕሩ ላይ ኃይለኛ ነፋስን አመጣ መርከቧም ከአንድ ጎን ወደ ሌላ ጎን፤ ከላይ ወደ ታች እያለች አቅጣጫዋን ጠብቃ መሔድ አቃታት፤ ውኃውም ወደ መርከቧ ውስጥ መግባት ጀመረ፡፡
በመርከቧ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ሁሉ በጣም ፈሩ፤ መርከቧም ትሰጥማለች ብለው በጣም ተጨነቁ ሁሉም ሰዎች በከባድ ጭንቀት ላይ ሆነው እግዚአብሔር አምላክ ይኸንን ታላቅ ንፋስ የላከብን ምን መጥፎ ነገር ሰርተን ነው ብለው መጨነቅ ጀመሩ፡፡
ይኼ ሁሉ ነገር ሲሆን ግን ዮናስ እንቅልፍ ወስዶት ነበር፡፡ የመርከቧም አለቃ ወደ ዮናስ ሔዶ ቀሰቀሰው፡፡ «ይህን ከባድ የሆነ ንፋስ ያቆምልን ዘንድ ለአምላክህ ፀልይልን» አለው፡፡
ዮናስም ይህን ሲሠማ ለመርከቧ አለቃ ይህ ነገር የመጣው በእኔ ይሆናል ከአምላክ ለመደበቅ እየሞከርኩ ነበር እኔን አንስታችሁ ወደ ውኃው ብትጥሉኝ ንፋሱ እና የመርከቧ መናወጥ ሊያቆም ይችላል አላቸው፡፡ በመርከቧም የነበሩ ሰዎች ዮናስ እንደነገራቸው አደረጉ፡፡ ወደ ባህሩ ወረወሩት፡፡ ወዲያውም ባህሩ ፀጥ አለ፡፡ ንፋሱም ቆመ፡፡
እግዚአብሔር አምላክም ዮናስን የሚውጠው ትልቅ አሳን አዘጋጀ፡፡ ዮናስም በአሳው ሆድ ውስጥ ሦስት ቀን ቆየ፡፡ በአሣ ነባሪ ሆድ ውስጥ ሆኖ ፀለየ እግዚአብሔርን እንዲረዳው ለመነ፡፡ እግዚአብሔርም የለመኑትን መልካም ነገር ቶሎ የሚሰማ ስለሆነ ፀሎቱን ሰማውና አሳውን ደረቅ መሬት ላይ እንዲተፋው አዘዘው፡፡ ትልቁም አሣ በፍጥነት ትዕዛዙን ተቀብሎ በመሬት ላይ ተፋው፡፡
ዮናስም ምንም ሳይሆን ከትልቁ አሳ ውስጥ ስለወጣ አምላኩን አመሠገነ ወደ ተላከበትም አገር ወደ ነነዌ ወዲያውኑ ሄደ፡፡ ወደከተማዋ እንደገባ ድመፁን ከፍ አድርጎ ለህዝቡ «እግዚአብሔር በናንተ በጣም ተከፈቶባችኋል ምክንያቱም ከክፋ ሥራችሁ የተነሣ ነው፡፡» የነነዌ ህዝቦች ይዋሻሉ፣ ይምላሉ፣ ይሰርቃሉ፣ ሌላም ብዙ መጥፎ ነገር ያደርጉ ነበር፡፡ ዮናስም ከዚህ መጥፎ ሥራችሁ ካልተመለሳችሁ አገራችሁ ይጠፋል ብሏል እግዚአብሔር ብሎ ነገራቸው፡፡ የነነዌ ሰዎችም ይህንን ሲሰሙ በጣም ተጨነቁ፤ የሚሠሩትንም ክፋ ሥራ ትተው እግዚአብሔርን የሚያስደስት ነገር በመስራት ጥሩ ሰው መሆን ፈለጉ፡፡ ስለዚህም ምንም ምግብ ሳይበሉ እና ሳይጠጡ ለሦስት ቀናት ያህል ፆሙ፡፡ ሁሉንም መጥፎ ነገር መሥራት አቆሙ፡፡ መጥፎ ሥራቸውንም ሰውን በመውደድ፣ ታዛዥ በመሆን በመልካም ሥራ ቀየሩት፡፡ እግዚአብሔር አምላክም ጥሩ ሰዎች መሆናቸውን ሲያይ እጅግ በጣም ተደሰተባቸው ከተማቸውንም አላጠፋባቸውም ብሎ ወሰነ፡፡
አያችሁ ልጆች እግዚአብሔር አድርጉ ያለንን ሁሉ ማድረግ አለብን በአደጋና በአስቸጋሪ ቦታ ላይ ስንሆንም ፀሎት ማድረግ አለብን ይሔን ካደረግን እግዚአብሔር ይጠብቀናል፡፡
ልጆች እግዚአብሔር አምላካችን እኛ ከመጥፎ ሥራችን ተቀይረን ጥሩ ሰዎች እንድንሆን ሁል ጊዜ ይፈልጋል እና ጥሩ ሰዎች ለመሆን ጥረት እናድርግ እሺ ልጆች፡፡
ደህና ሰንብቱ!!
Contact Us

በ Facebook ያግኙን
የተዋህዶ ልጆች
ጾም ማለት ሰውን ከምግብ መከልከል ነው፡፡ ፍት.አን.15 “ጾምሰ ተከልኦተ ብዕሊ ዕምመብልዕ በጊዜ እውቅ” ጾም ማለት በታወቀው ዕለት በታወቀው ሰዓት ሰው ከምግብ የሚከለከለው መከልከል ነው፡፡ መብል መጠጥ...
ዳግም ምጽአት ‹‹ደገመ›› እና ‹‹መጽአ›› ከሚሉ ሁለት የግዕዝ ግሦች የተዋቀረ ሐረግ ነው፡፡ የጌታችንንና የአምላካችንን ለሁለተኛ ጊዜ ወደዚህች ዓለም መምጣት ያመለክታል፡፡ የክርስቶስ ዳግም ምጽአት ዳግምነቱ ለልደቱ ነው፡፡ ማለትም ልደቱን ‹‹ቀዳማዊ ምጽአት›› ካልን ዘንድ ለፍርድ መምጣቱን ‹‹ዳግም ምጽአት›› እንላለን፡፡
የምንሠራውና የምናሻሽለው አይደለም ከታኅሣሥ 29 ቀን ጀምሮ እስከ ዐቢይ ጾም መግቢያ ድረስ ያለው ወቅት /ጊዜ/ ዘመነ አስተርእዮ /የመገለጥ ወራት/ እየተባለ ይጠራል፡፡ በታኅሣሥ 29 ቀን የጌታችን ልደት ስለሆነ በዚህ አምላክ በሥጋ የተገለጠበት በዓል ይከበራል፡፡ ጥር 11 ቀን ደግሞ በጌታችን ጥምቀት የሥላሴ አንድነት ሦስትነት በይፋ የተገለጠበት ነው፡፡
1. ጸሎተ ነግህ
2.ጸሎተ ሠለስት
3.ቀትር(6 ሰዓት)
4.ተሰዓተ ሰዓት (9 ሰዓት)
5.ጸሎተ ሰርክ (11 ሰዓት)
6.ጸሎተ ንዋም (የመኝታ ጊዜ ጸሎት)
7.መንፈቀ ሌሊት (እኩለ ሌሊት)